1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢትዮጵያ የሰባዊ እርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃግብር በጀኔቭ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2016

በኢትዮጵያ በድርቅ፤ ጎርፍና ጦርነት ምክኒያት ለከፍተኛ ችግር የተዳረጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ትናንት ሲዊዘርላንድ ጀኔቭ በተዘጋጀ መርሃ ግብር፤ ከለጋሾች 630 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ተገለጸል።

https://p.dw.com/p/4etQH
በጄኔቭ የተመድ ጽሕፈት ቤት
በጄኔቭ የተመድ ጽሕፈት ቤት ምስል Salvatore Di Nolfi/KEYSTONE/picture alliance

እርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃግብር በጀኔቭ

 

በተደጋጋሚ የሚከስተው ሰብአዊ ቀውስ ምክንያቶች

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ዋና ጸሐፊ ጆየ ምሱያ በመርሃግብሩ ላይ ባሰሙት ንግግር፤ በኢትዮጵያ ያለው ችግር፤ በተደጋጋሚ የሚከሰቱት ድርቅ ጎርፍና ጦርነት የፈጠሩት መሆኑን በመግለጽ፤ ህዝቡ በአሁኑ ወቅት ለክፍተኛ ችግርና አደጋ ተጋልጦ እንደሚገኝ ገልጸዋል። «በኢትዮጵያ ግጭትና የአየር ንብረት ለውጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እርዳታ ጠባቂ አርጓቸዋል» በማለትም የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ከመቼውም ግዜ በላይ የለጋሾችን ተጨማሪ እርዳታ የሚያስጠይቅ መሆኑን አስታውቀዋል። በተደጋጋሚ የሚከሰቱት ድርቅ፤ ጎርፍና ጦርነት ኢትዮጵያውያንን ለምግብ እጥረትና ለተለያዩ ችግሮች የሚያጋልጡ ዋናዎቹ ምክንያቶች መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ዋና በጸሐፊ ምሱያ፤ በአሁኑ ወቅት በተለይም ከሚቀጥለው ሐምሌ እስከ መስከረም ወር ድረስ 10.8 ሚሊዮን ህዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የሚጋለጥ መሆን አስገንዝበዋል። በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሆኑ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች በአገሪቱ እንደሚገኙና እነሱም አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ያለው ሰባዊ ቀውስና ችግር አሳስቢነት

በቅርቡ ኢትዮጵያን እንደጎበኙና ያለውን ችግር በቅርብ እንደታዘቡ የገለጹት የመርሃግብሩ ተባባሪ አዘጋጅ አገር ብርታኒያ፤ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሴክሬታሪ ሚስተር አንድሬው ማይክል በበኩላቸው ፤ በኢትዮጵያ አሰቃቂ ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት መድረስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። «በኢትዮጵጵያ ያለው ሁኒታ የሚያሳየው ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ ያለብን መሆኑና፤ ሕይወት ለማትረፍም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግ ነው» በማለት፤ አገራቸው ለአሁኑ አስቸኳይ ሁኒታ 100 ሚሊዮን ፓውንድ የለገሰች መሆኑን አስታውቀዋል።

ከለጋሾች የተገኘው የእርዳታ ገንዘብ መጠን

ሌሎች በፕሮግራሙ የተገኙና በቪድዮ የተካፈሉ የ21 ለጋሽ አገሮች ተወካዮችም በየበኩላቸው ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ፤ በተለያዩ መርሃግብሮች በኩል እየስጧቸው ካሉ እርዳታዎች በተጨማሪ ለአሁኑ የስቸኳይ እርዳታ መንግሥቶቻችው የለገሱትን የገንዘብ መጠን አስታውቀዋል። ከአሜርካ 253 ሚሊዮን ዶላር፤ ከአውሮፓ ሕብረትና አባል መንግሥታት 139 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በድምሩ በትናንትናው መርሀ ግብር  630 ሚሊየን  ዶላር መገኘቱ ታውቋል። ሆኖም ግን ይህ መጠን የመንግሥታቱ ድርጅት ለኢትዮጵያ ከሚያስፈልገውና ከጠበቀው አንድ ቢሊዮን ዶላር በታች እንደሆነና ይህም በአሁኑ ወቅት በሌሎች እንደ ሱዳን ጋዛ የመሳሰሉ አገሮችም ተመሳሳይ የእርዳታ ጥሪዎችም ያሉ በመሆኑ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።

ድርቅ ትግራይ ክልል
በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የትግራይ ክልል ምስል Mariel Mueller/ Haileselassie Million/DW

መርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች የተሰጡ አስተያየቶችና ቅሬታዎች

በመርሃ ግብሩ የታደሙ ለጋሽ አገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በሰጧቸው ተጨማሪ አስተያየቶችም ፤ ኢትዮጵያ ለችግር የምትጋለጥባቸውን ምክንያቶች ጦርነትና ግጭት የመሳሰሉትን በማስወገድ ሰላም መፍጠርና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በማክበር፤ ከሁልግዜ የእርዳታ ጠባቂነት ልትላቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ችግር ልዩ ባህሪ

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ምክትል ዋና ጸሐፊ ወይዘሮ ምሱያ አክለውም፤ የኢትዮጵያ ችግር ከሌሎች የሚለይበትንና ምናልባትም የሚከፋበትን ዘርዝረው አስረድተዋል። «አንደኛ የሚፈጠሩት ሰብአዊ ቀውሶች ሁልጊዜ ካለፈው የባሱ ነው የሚሆኑት። በችግር የሚጠቁት ሰዎች ቁጥርም እያደገ ነው የሚሄደው፤ ሁለተኛ  ኢትዮጵያ በአየር ንበረት ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቁት አገሮች ውስጥ ናት። ድርቅም ጎርፍም የሚፈርረቁባ ነች። ሦስተኛ፤ በየግዜው የሚከሰቱ ጦርነቶችና ግጭቶች የተጎጂዎችንና እርዳታ ጠባቂዎችን ቁጥር እንዲጨምር ያደርገዋል» በማለት  ችግሩን ለማቀለል የአጭር ግዜ የእርዳታና የረጅም ጊዜ የልማት ዕቀድ የሚያስፈልግ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

መርሃ ግብሩ መዝጊያ መርሀ ግብር

በመጨረሻም የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አምሳደር ታየ አጽቀ ሥላሴ ከለጋሾች ለተገኘው እርዳታና ድጋፍ አመስግነው፤ የተሰጡ አስተያየቶችንና የተነሱ ቅሬታዎችን እንደሚወሰዱና መንግሥታቸው እንደሚሠራባቸው በመግለጽ፤ ህዝባቸውን የመመገብና ከችግር የማላቀቅ ሀላፊነት በቅድሚያ የሚወድቀው በመንግሥት ስለመሆኑ መረዳት እንዳለና፤ በዚህ ላይ በመሥራትም  መንግሥታቸው ረህብን ታሪክ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል ።

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ