1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ምዕናባዊ ኦቲዝም፤ የዲጅታል ዘመን ልጆች ስጋት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2016

ባለሙያዎች እንደሚሉት በተንቀሳቃሽ ስልኮች፣በታብሌት፣በቴሌቪዝን እና በሌሎች ዲጅታል መሳሪያዎች ላይ ረዘም ያለ ጊዜ የሚያሳልፉ ልጆች ለጭንቀት እና ለመረበሽ፣ ለትኩረት ማጣት፣ ለንግግር እና ለቋንቋ መዘግየት እንዲሁም ለግንዛቤ እድገት ውሱንነት ይዳረጋሉ። የሰዎችን ስሜት የመረዳት እና የመግባባት ችሎታቸውንም ይቀንሳል።

https://p.dw.com/p/4erN2
እንደ ዓለም አቀፉ  የጤና ድርጅት ከ 5 አመት በታች የሆኑ ህጻናት በቀን ከ 60 ደቂቃዎች በላይ በስማርት ስልኮች፣ በኮምፒተር ወይም በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ማሳለፍ የለባቸውም።
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ከ 5 አመት በታች የሆኑ ህጻናት በቀን ከ 60 ደቂቃዎች በላይ በስማርት ስልኮች፣ በኮምፒተር ወይም በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ማሳለፍ የለባቸውም።ምስል Lev dolgachov/Zoonar/picture alliance

ምናባዊ ኦቲዝም በልጆች አጠቃላይ እድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አለው


የያዝነው የጎርጎሪያኑ ሚያዚያ ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ  የእድገት ውሱንነትን /ኦቲዝም/በተመለከተ ግንዛቤ የሚሰጥበት ወር ነው።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት እንደ ሞባይል፣ ታብሌት እና ቴሌቪዝንን የመሳሰሉ ዲጅታል ቴክኖሎጅዎችን አብዝቶ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ በልጆች ላይ በሚከሰተው ምዕናባዊ ኦቲዝም ላይ ያተኩራል።
ባለንበት የዲጅታል ዘመን ቴክኖሎጂ በሰው ልጆች ህይወት ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ቴክኖሎጂ ተግባቦትን እና የመጓጓዣ ዘዴን  በማሻሻል ህይወትን ቀላል እና ምቹ  እያደረገ ይገኛል።ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ በማድረግ፣ የጤና አገልግሎትን በማሻሻል፣ንግድ እና አስተዳደርን የተሳለጠ በማድረግ ቴክኖሎጂ ዓለምን ትንሽ እና የተሻለ የመኖሪያ ቦታ እያደረገ ነው።የበይነመረብ፣ የተንቀሳቃሽ ስልኮች እና የኮምፒዩተሮች ወደ ዲጅታል ቴክኖሎጂው መምጣት ደግሞ፤ የሰዎችን ግንኙነት በማሻሻል የአኗኗር ዘይቤን በጎ በሆነ መልኩ ለመለወጥ  አስተዋጽኦ አድርጓል። ከዚህ አኳያ ቴክኖሎጂ በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ ጠቃሚ እና አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል። 
ያም ሆኖ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም  በአግባቡ እና ጥንቃቄ የታከለበት ካልሆነ  ይዟቸው የሚመጣ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖዎችም አሉት። ከነዚህም መካከል በልጆች አስተዳደግ እና ጤና ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ አንዱ ነው። የህፃናት እድገት ባለሙያ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር  አፀደ ተክለሀይማኖት  እንደሚሉት በተለይ ከ5 ዓመት በታች ባሉ አዳጊ ህፃናት የአእምሮ ዕድገት ላይ ከፍተና ጫና አለው።

በምዕናባዊው ዲጅታል ዓለም  ለረጅም ጊዜ  የሚቆዩ ልጆች የጭንቀት እና የመረበሽ እንዲሁም ምዕናባዊ  መስተጋብር እና እውነታን ለመለየት ሊቸገሩ ይችላሉ
በምዕናባዊው ዲጅታል ዓለም ለረጅም ጊዜ  የሚቆዩ ልጆች የጭንቀት እና የመረበሽ እንዲሁም ምዕናባዊ  መስተጋብር እና እውነታን ለመለየት ሊቸገሩ ይችላሉምስል Channel Partners/Zoonar/picture alliance

ምዕናባዊ ኦቲዝም ምንድነው?

ቴክኖሎጂ የሕይወታችን አካል እየሆነ በመጣበት በዚህ የዲጅታል ዘመን፣ በልጆች እድገት ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድር መረዳት አስፈላጊ ነው። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዓለም አቀፉ  የጤና ድርጅት (WHO) በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆችን የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀምን  በተመለከተ  በወጣው ዘገባ፤  ከ 5 አመት በታች የሆኑ ህጻናት በቀን ከ 60 ደቂቃዎች በላይ በስማርት ስልኮች፣ በኮምፒተር ወይም በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ማሳለፍ የለባቸውም። ከ ሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ደግኖ ፈፅሞ ለስክሪን ፊት  መቀመጥ የለባቸውም። ልጆች ከኤሌክትሮኒክስ ይልቅ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ወይም በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያሉ ግንኙነቶችን ለምሳሌ ተረቶችን ማዳመጥ ወይም ማንበብን በመሳሰሉ ተግባራት መቀየርን ድርጅቱ ይመክራል። ይህም ሁለንተናዊ እድገታቸው እንዲዳብር ይረዳል።

ልጆች ከዲጅታል መሳሪያዎች ይልቅ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ወይም በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያሉ ግንኙነቶችን ለምሳሌ ከተንከባካቢዎች ጋር ታሪኮችን ማዳመጥ ወይም ማንበብን በመሳሰሉ ተግባራትን እዲከውኑ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ልጆች ከዲጅታል መሳሪያዎች ይልቅ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ወይም በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያሉ ግንኙነቶችን ለምሳሌ ከተንከባካቢዎች ጋር ታሪኮችን ማዳመጥ ወይም ማንበብን በመሳሰሉ ተግባራትን እዲከውኑ ባለሙያዎች ይመክራሉ።ምስል Carl Recine/REUTERS

ይህንን ባለመገንዘብ የልጆችን ዕድሜ ባላገናዘበ  መልኩ ከመጠን በላይ የዲጅታል ቴክኖሎጅ መሳሪያዎችን እንዲጠቀሙ መፍቀድ ግን ለእድገት ውሱንነት እንደሚያጋልጥ ባለሙያዋ ገልፀዋል። በተለይ ምዕናባዊ ኦቲዝም/Virtual Autism  /በዲጂታል ዘመን ለአዳጊ ልጆች አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ችግር ሲሆን በኢትዮጵያም በተለይ ከኮሮና ወረርሽኝ ወዲህ በስፋት መታየቱን ገልፀዋል። ባለሙያዋ እንደሚሉት ምዕናባዊ ኦቲዝም  ከመጠን ያለፈ የስክሪን ጊዜ ወይም  የዲጅታል መሳሪያዎች አጠቃቀም በህጻናት እድገት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያመለክት ነው። ለልጆች አደገኛ የሆኑ መተግበሪያዎች የትኞቹ ናቸው?

የምዕናባዊ ኦቲዝም ምክንያቶች

ከዚህ አኳያ ስማርት ስልኮች፣ ታብሌቶች፣ ኮምፒውተሮች እና ቴሌቪዥንን ጨምሮ ከመጠን ላለፈ የስክሪን ጊዜ የተጋለጡ ልጆች ለምዕናባዊ ኦቲዝም የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው ልጆች በገሃዱ ዓለም ውስጥ ለመሳተፍ በቂ እድሎችን ስለማያገኙ፤ከወላጆች፣ ከተንከባካቢዎች እና ከእኩዮቻቸው ጋር ፊት ለፊት ለሚደረጉ ግንኙነቶች፣አስፈላጊ ለሆኑ ማህበራዊ ክህሎቶች እና ለስሜት እና ለግንዛቤ እድገታቸው እንቅፋት ይሆናል። በአካላዊ ጨዋታ እና ከቤት ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚያሳልፉትን ጊዜ በመቀነስም በአዳጊዎች የስሜት  ሚዛን ላይ መዛባትን ያስከትላል። ይህም አጠቃላይ እድገታቸውን በመጉዳት ለምዕናባዊ ኦቲዝም ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። 

 እንደ ባለሙያዎች የዲጅታል ቴክኖሎጅ መሳሪያዎችን አብዝተው እንዲጠቀሙ መፍቀድ ልጆችን ለእድገት ውሱንነት ያጋልጣል።
 እንደ ባለሙያዎች የዲጅታል ቴክኖሎጅ መሳሪያዎችን አብዝተው እንዲጠቀሙ መፍቀድ ልጆችን ለእድገት ውሱንነት ያጋልጣል።ምስል Georg Wendt/dpa/picture alliance

የምዕናባዊ ኦቲዝም ምልክቶች ምን ምን ናቸው?

ዶክተር አፀደ እንደሚሉት ከልክ ባለፈ የስክሪን ጊዜ እና የዲጂታል አጠቃቀም ሳቢያ በልጆች ላይ የሚከሰተው ምዕናባዊ ኦቲዝም፤ በህጻናት እድገት ላይ ተፅዕኖ የሚያመጡ የተለያዩ ምልክቶች ይኖሩታል። 
ከነዚህም መካከል ዶክተር አጸደ እንደሚገልፁት ከምዕናባዊው ዓለም ውጭ ባለው ውስን ማህበራዊ መስተጋብር ምክንያት የንግግር እና የቋንቋ እድገት እክሎች ማጋጠም፣ በዕድሜያቸው  የተለመደ ነው ተብሎ ከሚታሰበው በላይ እንቅስቃሴ ማድረግ እና እረፍት ማጣት፣ በአንድ የተወሰነ እንቅስቃሴ ወይም ውይይት ላይ ትኩረትን ረዘም ላለ ጊዜ ለማቆየት መቸገር ወይም ማተኮር  አለመቻል ይጠቀሳሉ።

ከአቻዎቻቸው ጋር ለመግባባት እና መስተጋብር ለመፍጠር መቸገር፣ከሰዎች የሰሟቸውን ቃላት መደጋገም፣ ለአንዳንድ ድምፆች፣ ሽታዎች እና ገፅታዎች «ሴንሲቲቭ» መሆን ወይም የተለዬ ምላሽ መስጠት።ለምሳሌ ድምፁን ሲሰሙ ጀሯቸውን የመያዝ ሁኔታ እንደሚያሳዩ ዶክተር አፀደ ገልፀዋል።
በገሃዱ ዓለም ከሚደረጉ መስተጋብሮች  ወይም የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ይልቅ ለምናባዊ እንቅስቃሴዎች ጠንካራ ፍላጎት ማሳየትም ሌላው ምልክት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ፣ ተደጋጋሚ ብስጭት እና ቶሎ መቆጣት ከምናባዊው አካባቢ ወደ እውነተኛ ህይወት ለመሸጋገር መቸገር፣  እና በስሜት ላይ ድንገተኛ እና ጉልህ ለውጦችን የማሳየት ባህሪም ተጠቃሾች ናቸው።

 ምዕናባዊ ኦቲዝም በልጆች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት 

ምናባዊ ኦቲዝም በልጆች አጠቃላይ ደህንነት እና እድገት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው። ስክሪንን ከመጠን በላይ መጠቀም ወደ ኦቲዝም እንደሚያመራም ጥቂት ጥናቶች ጠቁመዋል። ከዚህ ባሻገር  ከመጠን ያለፈ የስክሪን ጊዜ እና ዲጂታል መስተጋብር  በልጆች ላይ የሌሎችን ስሜት  የመረዳት እና የመሳሰሉትን አስፈላጊ ማህበራዊ ክህሎቶችን ለማዳበር እንቅፋት ይፈጥራል። በምናባዊ አካባቢዎች ውስጥ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ የፊት-ለፊት መስተጋብርን ይቀንሳል፣ ይህም ትርጉም ያለው ግንኙነት ለመመስረት እና ከሰዎች ጋር ያላቸውን የስሜት ትስስር እና የመግባባት ችሎታቸውን ሊያደናቅፍ ይችላል።ማህበራዊ መስተጋብሮችን ይቀንሳል።ትኩረት የሚሻዉ የልጆች ችግር
ከግንዛቤ እድገት አኳያም፤በተንቀሳቃሽ ስልኮች ፣በቴሌቪዝን እና ሌሎች ዲጅታል መሳሪያዎች ላይ በሚመለከቷቸው ምናባዊ ተሞክሮዎች  ላይ ብቻ የታጠሩ ታዳጊዎች ከዕውነተኛው ዓለም  ጋር  ያላቸው መስተጋብር  ውስን ይሆናል፤ ይህም ለንግግር መዘግየት ችግር  ይዳርጋል።በገሃዱ ዓለም በሚከናወኑ ተግባራት ላይም ለማተኮር መቸገርን ያስከትላል።

እንደ ዓለም አቀፉ  የጤና ድርጅት ከ 5 አመት በታች የሆኑ ህጻናት በቀን ከ 60 ደቂቃዎች በላይ በስማርት ስልኮች፣ በኮምፒተር ወይም በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ማሳለፍ የለባቸውም። ከ ዓንድ ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ደግሞ ፈፅሞ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ፊት መቀመጥ የለባቸውም።
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ከ 5 አመት በታች የሆኑ ህጻናት በቀን ከ 60 ደቂቃዎች በላይ በስማርት ስልኮች፣ በኮምፒተር ወይም በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ማሳለፍ የለባቸውም። ከ ዓንድ ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ደግሞ ፈፅሞ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ፊት መቀመጥ የለባቸውም። ምስል AFP

ስሜት ደህንነት አንፃርም፤ ለምናባዊ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜ  የሚጋለጡ  አዳጊዎች የጭንቀት እና የመረበሽ እንዲሁም ምዕናባዊ  መስተጋብር እና እውነታን ለመለየት ሊቸገሩ ይችላሉ። ከሰዎች ጋር ፊትለፊት የሚያደርጉት መስተጋብር የተገደበ  በመሆኑም፤ የሌሎችን ስሜት የመረዳት እና የመገንዘብ ችሎታቸውም ይቀንሳል።
አካላዊ ጤንነትን በተመለከተም፤ከዲጂታል መሳሪያዎች ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ማሳለፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ስለሚቀንስ ልጆችን  እንደ ውፍረት ላሉ እና ከጤና ችግሮች ጋር ወደ  ተያያዙ የአኗኗር ዘይቤዎች  ይመራል። ልጆች በተለይ ከመኝታ ጊዜ በፊት የሚያሳልፉት ከመጠን በላይ የሆነ የስክሪን ጊዜ፣ የእንቅልፍ ሁኔታቸውን በመረበሽ፤ በአጠቃላይ ጤንነታቸው እና ደህንነታቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
የዲጂታል መሳሪያዎችን ከመጠን በላይ መጠቀም የወላጅ-እና የልጅ ትስስርንም ይቀንሳል።በትምህርት አቀባበል ላይም ተፅዕኖ ያሳድራል።
ለመሆኑ ምዕናባዊ ኦቲዝም ከሌላው የአእምሮ እድገት ውሱኑንነት ወይም ኦቲዝም በምን ይለያል?

«ልዩነታቸው ኦቲዝም የታወቁ መነሻ ምክንያቶች ባይኖሩትም የበዛ የስክሪን ጊዜ ያባብሰዋል እንጅ መነሻ አይለም።የምዕናባዊ ኦቲዝም ግን መነሻው ለብዙ ስዓት ስክሪን ላይ በማሳለፍ የሚመጣ በመሆኑ መከላከል የምንችለው በመሆኑ ከኦቲዝም ይለያል ። ከተከሰተ በኋላም በተለያዩ ህክምናዎች ምልክቶቹን የመመለስ እና የማሻሻል ዕድላችን የተሻለ ነው የሚሆነው። » ብለዋል።

ምዕናባዊ ኦቲዝምን እንዴት ማከም ይቻላል?

ስለሆነም  ምዕናባዊ ኦቲዝምን በልጆች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ  የስክሪን ጊዜ ገደቦችን ማበጄት ፡ ወይም አጠቃቀሙ ከልጆች ዕድሜ ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዋ ገልፀዋል።

በተንቀሳቃሽ ስልኮች ፣በቴሌቪዝን እና ሌሎች ዲጅታል መሳሪያዎች ላይ በሚመለከቷቸው ምናባዊ ተሞክሮዎች  ላይ ብቻ የታጠሩ ታዳጊዎች ለዕውነተኛው ዓለም የቋንቋ መስተጋብር ያላቸው ተጋላጭነት ውስን ነው
በተንቀሳቃሽ ስልኮች ፣በቴሌቪዝን እና ሌሎች ዲጅታል መሳሪያዎች ላይ በሚመለከቷቸው ምናባዊ ተሞክሮዎች  ላይ ብቻ የታጠሩ ታዳጊዎች ለዕውነተኛው ዓለም የቋንቋ መስተጋብር ያላቸው ተጋላጭነት ውስን ነውምስል Gaelle Girbes/Getty Images

ከዚህ ባሻገር አማራጭ እንቅስቃሴዎችን ለምሳሌ ከቤት ውጭ መጫወት፣ ማንበብ እና የልጆችን ፈጠራ  ማበረታታት ጠቃሚ ነው። ማህበራዊ ግንኙነቶችን ማበረታታት፡ ማህበራዊ ክህሎቶችን እና ስሜታዊ እድገትን ለማሳደግ ከቤተሰብ አባላት፣ እኩዮች እና ተንከባካቢዎች ጋር ፊት-ለፊት መስተጋብርን መፍጠርም ያስፈልጋል።
የልጆች መንከባከቢያ ቦታ በተቻለ መጠን  የግንዛቤ፣ የስሜት እና አካላዊ እድገትን የሚደግፍ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ልጆችን ለእንቅስቃሴ የሚጋብዝ ቢሆን ይመረጣል።  

ስለ ምዕናባዊ ኦቲዝም ትክክለኛ ግምገማ በማድረግም በችግሩ ላይ መፍትሄ ለመፈለግ  የጤና ባለሙያዎችን ማማከር  እና ልጆችን ወደ ጤናማ  ሁኔታ የሚመልሱ  የተለያዩ ህክምናዎችን መከታተልም አስፈላጊ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰሯ ገልፀዋል።
ይህንን ችግር መረዳትም ወላጆች፣ ተንከባካቢዎች እና ማህበረሰቡ የመጭውን ትውልድ ጤናማ እድገት ለማረጋገጥ እንደ ባለሙያዋ ረዳት ፕሮፌሰር  አፀደ ተከለሀይማኖት አስፈላጊ ነው።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ 
ሂሩት መለሰ