1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አስከሬን አግኝተን መቅበር አልቻልንም» የሟቾች ቤተሰብ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2016

ባለፈው ሳምንት ዓርብ አዲስ አበባ ውስጥ የተገደሉት የፋኖ አባላት አስከሬን እስካሁን ለቤተሰብ አለመሰጠቱን የሟቾች ቤተሰቦች ተናገሩ። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የቤተሰብ አባላት ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ከፌዴራል ፖሊስ እስከ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢመላለሱም የሟቾቹን አስከሬን ተረክበው ለመቅበር አለመቻላቸውን አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/4etMd
News Mag 1 Transportation
ባለፈው ሳምንት ዓርብ አዲስ አበባ ውስጥ የተገደሉት የፋኖ አባላት አስከሬን እስካሁን ለቤተሰብ አለመሰጠቱን የሟቾች ቤተሰቦች ተናገሩ። ፎቶ ከማኅደር፤ አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

«አስከሬን አግኝተን መቅበር አልቻልንም» የሟቾች ቤተሰብ

ባለፈው ዓርብ ሚያዚያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ቦሌ በተለምዶ ሚሊኒየም አዳራሽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በፖሊስ ክትትል ስር የነበሩ የፋኖ አመራር እና አባላት ያሏቸውን ናሁሠናይ አንዳርጌ እና አቤኔዘር ጋሻው የተባሉ ወጣቶች በተደረገው የተኩስ ልውውጥ መገደላቸውን አሳውቋል።

የቤተሰብ አስከሬን ጥየቃ እንግልት

ከዚያ ቀን ማግስት ጀምሮ እስከ ዛሬ ባሉት አምስት ቀናት ቤተሰብ አስከሬናቸውን ማግኘት ከባድ ሆኖበታል ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የገለለጹት አንድ የቤተሰብ አባል ከሟቾቹ ወጣቶች አንዱ የሆነው የናሁሠናይ እናት ወ/ሮ ሐረገወይን አዱኛ የልጃቸውን አስከሬን ለማግኘት ወደ ፖሊስ ቢመላለሱም እስካሁን አልተሳካም ብለዋል።

«እስካሁን ድረስ ምንም አዲስ ነገር የለም። ቅዳሜ እናት የአስከሬን ፍለጋውን የጀመሩት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ነው፡፡ እነሱ አይመለከተንም ሲሏቸው ወደ ፌዴራል ፖሊስ ነው የሄዱት፡፡ ከዚያን ለሰኞ ብትቀጠርም ትናንትም አልቅሳ ነው የገባችው፡፡ ብትገባም የሚያናግራት ጠፍቶ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ሂዱና ጠይቁ ነው የተባሉት፡፡ ከዚያም መልስ ስታጣ ተመልሰው ወደ ፌዴራል ፖሊስ ሲሄዱ አስከሬኑን ያነሳው አዲስ አበባ ፖሊስ በመሆኑ ወደዚያው ሂዱ ተባሉ፡፡ ዛሬ ወደዛው ሄደዋል መልስ እየተጠበቀ ነው።» ሲሉ ባለፉት አምስት ቀናት ያሳለፉትን እንግልት ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ ሁለቱ ወጣቶች የተገደሉት «ሽብር ለመፈጸም ስንቀሳቀሱ ፖሊስ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም ከፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ ወደ ማድረግ በመግባታቸው ነው» ብሏል፡፡ ፖሊስ በዕለቱ ወጣት አቤነዘር በተኩስ ልውውጡ ሕይወቱ ወዲያው ሲያልፍ ወጣት ናሁሠናይ ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ ሳለ ሕይወቱ አልፏል ማለቱም አይዘነጋም።

አዲስ አበባ መሀል ከተማ
አዲስ አበባ መሀል ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

ስርዓተ ቀብሩን የሚጠባበቀው ዘመድ አዝማድና የአካባቢው ማኅበረሰብ

አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የቤተሰብ አባል አሁን ላይ ቤተሰብ አስከሬኖቹን ወስደው ስርዓተ ቀብሩን መፈጸም ባለመቻሉም ጭንቀት ውስጥ ነን ብለዋል። «በሕይወት ያለ ሰው ብሆን ለመረጃ ይባላል።፡ በሕይወት የሌለን ሰው ማቆየት ለምን እንደሆነ አልተረዳንም።» ያሉት እኚህ የቤተሰብ አባል ቅዳሜ ዕለት አስከሬን ለመውሰድ በተሰጠው ቀጠሮ መሠረት ወደ ስፍራው ያቀኑት ሁለት ወጣቶች በፖሊስ መታሰራቸውንመም አስረድተዋል። በዚህ መሃል ከአዲስ አበባም ሆነ ከጎንደር ቤተሰብ ለቅሶ ለመቀመጥም ግራ መጋባት መፈጠሩንም አክለው አብራርተዋል።

የሟች ወጣት ናሁሠናይ የቅርብ ቤተሰብ መሆናቸውን የገለጹት እኚህ አስተያየት ሰጪ የሟቹ እናት በዚሁ አዲስ አበባ በህክምና ላይ ሳሉ ክስተቱ መፈጠሩንም አስረድተው አሁን ላይ «አስከፊ» ያሉት ሁኔታ ላይ ሆነው አስከሬን ፍለጋ እንደሚንከራተቱም ጠቅሰዋል።

«እሷ ከመሞቱ አንድ ሳምንት በፊት ነው ከጎንደር አዲስ አበባ የመጣችው። ከክስተቱ በኋላ ወደ ጎንደር የሄደ ቤተሰብ የለም። ከሄድንም አስከሬን ይዘን ነው የምንሄድ። እናት አሁን መናገር እንኳ የማትችልበት ሁኔታ ላይ ነች። አሁን ሀዘን ትተን ሌላ ሥራ ላይ ነን ማለት ነው። አንድ ልጇን አጥታ ለመቅበር እንኳ ላልቻለች እናት ሀዘኑ ከባድ መሆኑ ይታወቃልና ካባድ ሁኔታ ውስጥ ናት እሷ» ሲሉ የቤተሰቡንም ሁኔታ አስረድተዋል።

ዶቼ ቬለ ስለጉዳዩ ለመጠየቅ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባዮች ቢደውልም ለዛሬ መረጃውን ማግኘት አልተቻለም። የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል «በአዲስ አበባ በህቡዕ የተደራጀው ፅንፈኛ ቡድን» ባላቸው ላይ እርምጃ መውሰዱን ባስረዳበት በዓርብ ዕለት መግለጫው፤ ናሁሠናይ አንዳርጌ ታረቀኝ እና አቤነዘር ጋሻው አባተ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ሲገደሉ ሀብታሙ አንዳርጌ ተሰማ ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን መግለጹ ይታወሳል። ግብረኃይሉ «በአዲስ አበባና አካባቢዋ ተወጥኖ ከሸፈ» ላለው «የሽብር ጥቃት እንዲፈጽሙ የመለመላቸው ወጣቶች ስልጠና» ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እይታ ውጭ አልነበረም ሲል ማሳወቁም አይዘነጋም።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ