1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንድ ዓመት የሆነዉ የሱዳኑ ጦርነትና ያስከተለዉ ሰብዓዊ ቀዉስ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 5 2016

የሱዳን ጦር ሰራዊት መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ ቡርሃንና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጭ ኃይል አዛዥ ጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ የአፍሪቃን ሦስተኛ ትልቅ ሀገር እና ሰፊ ሃብት ለመቆጣጠር ዛሬም እየተዋጉ ነው። በዚህ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። እንደ ተመድ ገለፃ ወደ 18 ሚልዮን የሚጠጉ ሱዳናዉያን ከፍተኛ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

https://p.dw.com/p/4ehn6
የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለዉ ሰብዓዊ ቀዉስ
የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለዉ ሰብዓዊ ቀዉስምስል Mohamed Zakaria/MSF/REUTERS

አንድ ዓመት የሞላዉ የሱዳኑ ጦርነትና የሰብዓዊ ቀዉስ

አንድ ዓመት የሞላዉ የሱዳኑ ጦርነትና የሰብዓዊ ቀዉስ

በሱዳን በሃገሪቱ ጦር ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰዉ ጦርነት በሃገሪቱ  ከ25 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ማብቂያ ለሌለው ሰብዓዊ ቀውስ ዳርጎታል። ጦርነቱ አንድ ዓመት የሞላዉ ቢሆንም ዛሬም ቀዉሱ ማብቂያ ያገኘ አይመስልም። የሱዳን ጦር ሰራዊት መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጭ ኃይል አዛዥ ጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ የአፍሪቃን ሦስተኛ ትልቅ ሀገር እና ሰፊ ሃብት ለመቆጣጠር ዛሬም እየተዋጉ ነው። ሁለቱ የሱዳን ጀነራሎች በሚፋለሙበት በዚህ ደም አፋሳሽ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ ሃገሪቱን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀዉስ ዉስጥ አስገብተዋል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለፃ በሱዳን ወደ 25 ሚልዮን ሰዎች ማለትም የሃገሪቱ ግማሽ የሚሆነዉ ዜጋ እርዳታን ፈላጊ ሆንዋል፤ ወደ 18 ሚልዮን የሚጠጉ ሱዳናዉያን ከፍተኛ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል። በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በሲቪል አካባቢዎች ላይ ጥቃት እየፈፀሙም ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪዬሎ X በተባለዉ ማህበራዊ መገናኛ ገፃቸዉ ላይ ባስተላለፉት መረጃ  "የሱዳን ጦር በመላው ዳርፉር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በተጠለሉበት ኤል ፋሸር ላይ በፈፀሙት የቦምብ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፤ ብዙዎችም ለጉዳት ተዳርገዋል። "  

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ በኤል ጌዚራ ግዛት በሚገኙ መንደሮች ላይ በሰነዘረው ጥቃት ለሲቪል ሰዎች ሞት እና በሺዎች ለሚቆጠሩ መፈናቀል ምክንያት መሆኑን ልዩ መልክተኛዉ አክለዉ ገልጸዋል። ቶም ፔሪዬሎ  ቀደም ሲል በ X ማህበራዊ መገኛቸዉ ባስተላለፉት ሌላ መልዕክት "ይህ ወደ አንደኛ ዓመት የተቃረበዉ ጦርነት በሲቪል ነዋሪዉ ላይ ጥቃት እያደረሰ እና ለከፍተኛ ረሃብ እያዳረገ በመሆኑ ለሁላችንም እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ሆኖ መቅረብ አለበት" ሲሉ መግለፃቸዉም ይታወቃል።  

የሱዳን አስከፊ የውድመት ዓመት

በሱዳን የዛሬ ዓመት ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከ 8.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተፈናቅሏል፤ አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በአጎራባች ሃገራት ቻድና ደቡብ ሱዳን ተጠልለው ይገኛሉ። በሽዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ በደቡብ ሱዳን ሬንክ ወደምትባል የድንበር ከተማ ሸሽተዋል። ወደዚች የድንበር ከተማ በየቀኑ ስደተኞች በብዛት በመጉረፋቸዉ ምክንያት መጠለያ ካምፖቹ በሕዝብ ተጨናንቀዋል፤ ሁኔታዉ በጣም አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ለምሳሌ በመጠለያዉ ወደ 200 የሚደርሱ ሰዎች በአንድ የመጸዳጃ ቤት በመጠቀማቸዉ ከፍተኛ የንጽህና ጉድለት ተከስቶ ይታያል፤ ይህም የኮሌራ ታማሚዎች ሰዎች መጨመር እንዲሁም ከባድ የኩፍኝ ሕሙማን ቁጥር ተከስቷል። የእርዳታ ድርጅቶች ለቀናቶች ምግብና ውኃ ሳያገኙ በእግር የተጓዙ ተፈናቃዮችን እና ከፍተኛ የስሜት ቀውስ የደረሰባቸውን ቤተሰቦች ፍላጎት ለማሟላት እየታገሉ መሆኑም ተናግረዋል።

 ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የተፈናቀሉት ካሊዳ ኢብራሂም ሳላቲን በመጠለያ ጣብያዉ ሁኔታው አስከፊ መሆኑን ለ DW ገልጸዋል። "ያለምንም ፍራሽ እና ልብስ መሬት ላይ ነዉ የምንተኛዉ፤ የሚበላ ምግብ የለንም። ውኃ አለ ግን ንፁህ አይደለም። ታማሚ ህጻናት በአቅራቢያቸው የሚሄዱበት የህክምና ጣብያ የላቸዉም። ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነው"  

በጸሎት መካከል የታየ ተስፋ መቁረጥ

ከሱዳንዋ ኤል ጌዚራ ከተማ የተፈናቀለችዉ ፋቲም ዱካ በደቡብ ሱዳንዋ ሬንክ መጠለያ ካምፕ ትገኛለች ። በዚህ ዓመት የእስልምና ቅዱስ የረመዳን ወር ተስፋ መቁረጥ በታየበት፣ ጸሎት የተሞላ እንደነበር ለ DW ተናግራለች።  

"በመጠለያ ካምፑ የምንበላው ነገር ባይኖረንም በህይወት ለመቆየት እየታገልን ነው። በጾም ላይ የነበሩ ብዙ ሰዎች ጾማቸውን የሚያፈርሱበት ምንም ነገር አልነበራቸዉም። ረመዳን ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የሚያፈጥሩት በውኃ ነበር። ሌላው ቀርቶ የምናገኘዉ መድሃኒት ለራስ ምታት ማስታገሻ የሚሆን ብቻ ነዉ። ለደም ግፊትና ለስኳር በሽታ መከላከያ የሚሆኑ መድኃኒቶች የሉንም።"

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የረሃብ ማስጠንቀቅያ

የምግብ እርዳታ ለማግኘት የሚደረገዉ ተስፋ አስቆራጭ ረዥም ጥበቃ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ። የዩናይትድ ስቴትስ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪዬሎ በሱዳን ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይሰራጭ እና በመላ አገሪቱ ሰላማዊ ሰዎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ በማደናቀፍ ወንጀል ፈጽመዋል ሲሉ የሱዳን ጦር ሰራዊቱንም ሆነ የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጭ ኃይላቱን ወንጅለዋል። ይህ የተሰማዉ፤ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የምግብ ደህንነት ደረጃ መዳቢ ተቋም "በሱዳን የተስፋፋውን ሞት እና የኑሮ ውድነት ለመከላከል ብሎም በሃገሪቱ የሚታየዉን አውዳሚ የረሃብ ቀውስ ለመከላከል" አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ሲል ባስጠነቀቀበት ወቅት ነው።

በዓለም ከፍተኛ የተባለ መፈናቀል የታየበት የሱዳኑ ጦርነት
በዓለም ከፍተኛ የተባለ መፈናቀል የታየበት የሱዳኑ ጦርነት ምስል El Tayeb Siddig/REUTERS

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ዋስትናን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ባለሥልጣን ባለፈዉ ታኅሣሥ ወር ባወጣዉ የምርመራ መረጃ በሱዳን ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአስከፊ ረሃብ አፋፍ ላይ እንደሚገኙ ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ በሃገሪቱ በቀጠለዉ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት እርዳታዉን ማድረስ አልተቻለም።

የስደተኞች ቀውስ እየተባባሰ በሄደበት በሱዳን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ የሞራል ጫና እየገጠመው መሆኑም ተመልክቷል። "ከሁሉ ቀዳሚዉ የሰዎችን ሕይወት ማዳን ነው ... ያሉት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት የክልል ዳይሬክተር ማማዱ ዲያን ባልዴ ችግሩን ለመቅረፍ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ተናግረዋል። 

ጀምስ ሽማኑላ / አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ