1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕዝብ ለሕዝብ ግኑኝነት

ሐሙስ፣ ግንቦት 3 2015

"በተለይም በአማራና በትግራይ ሕዝብ መካከል ግንኙነቱን የማጠናከር ስራ መጀመር አለበት። ፖለቲከኞቹ ዱላውን ለሕዝቡ ይመልሱለትና ሕዝቡ የሚያደርገውን ያውቃል"

https://p.dw.com/p/4RDQJ
Armenien Papst Franziskus und Karekin II
ምስል picture alliance/AP Photo/L'Osservatore Romano

" ፖለቲከኞቹ ዱላውን ለሕዝቡ ይመልሱ"

በትግራይና በአማራ ሕዝቦች መካከል የተፈጠረዉን መቃቃር ለማቃለል በሁለቱ ክልሎች መካከል  የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጀመር እንዳለበት  የሁለቱ ክልሎች ተወላጆች የሆኑ የፓለቲካ አቀንቃኞች አሳሰቡ።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከፖለቲከኞች መጨባበጥ በዘለለ የሁለቱ ሕዝብ ግኑኝነት ወደ ቀድሞው እንዲመለስ የሐይማኖት አባቶች፣ ሙሁራንና የሐገር ሽማግሌዎች ቀዳሚውን ሚና መጫወት አለባቸው ። 

ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና እሱን ተከትለው በኬንያ በተደረጉ ስምምነቶች ቦኋላ በሰሜኑ የሐገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት ቆሞ አንጻራዊ ሰላም ቢገኝም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በተገቢው መንገድ አለመጀመሩ ብዙዎችን አሳስቧል። አቶ አዲስ ጌታነህ የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ አቀንቃኝ ናቸው። ፖለቲከኞቹ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኘነቱ አይፈልጉትም በማለት ይተቻሉ።

"ፖለቲከኞቹ ሕዝቡ እንደዚህ ተቃቅሮ ቢቆይ ደስ ይላቸዋል። ምክንያቱ አንድ የአማራ እናት እና አንድ የትግራይ እናት ተገናኝተው ቁጭ ብለው ሲያወሩ ምንድነው የሚነጋገሩት ስንል፤ ስለጉዳታቸው፣ በጸቡ ውስጥ እነሱን የሚመለከት ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለ ሲነጋገሩ አንድ ሌላ ነገር ይመጣል። ስለዚህ ሕዝቡ ተቃቅሮ ቢቆይ ፖለቲከኞቹ የሚጠሉት አይመስለኝም፤ እንዳውም ይፈልጉታል።"
በዳያስፖራው የትግራይ ማሕበረሰብ የፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑት ፕሮፌሰር መድሃኔ አስመላሽ በበኩላቻው የሰላም ስምምነቱ ወደ ሕዝብ ያልወረደው የፌደራል መንግስትና ህወሐት ቀደም ሲል ቆመንለታል ለሚሉት ሕዝብ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ካለማድረጋቸው ጋር ተያይዞ ሊከተል ከሚችል ተጠያቂነትን ለማምለጥ ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

Symbolbild Friedensbotschaft
ምስል Müller-Stauffenberg/IMAGO

"ሁለቱም ከፌደራልም ከትግራይ በኩልም ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊትና ከተጀመረም ቦኋላ የሚገቧቸው ቃሎች ነበሩ። በፌደራል መንግስት በኩል ህወሐት ዱቄት አደርግላችኋለሁ የሚል ዓላማ ከዳር አልደረሰም፤ ከህወሐት በኩል ደግሞ እነዚህ ትግራይን ለማጥፋት ስለመጡ ከተዋጋችሁ፣ ሕይወታችሁን ከሰጣችሁ ነገ ነጻ የሆነች ሃገረ ትግራይ ታያላችሁ የሚል ዓላማ ዳር ለማድረስ ዓላማ ነበረው። ሁለቱም ይህን ዓላማቸውን ዳር ማድረስ አልቻሉም። ይህን ዳር ለማድረስ ቢፈለግ ተመልሰህ ወደ ጦርነት ሊገባ ነው። ስለዚህ መሐል የሆነ መግባባት ላይ የመምጣት ነገር ይኖራል። ዓላማቸው አለማሳካታቸው የሕዝብን ጥያቄ ለማዳመጥ ጊዜ እንዲሰጡ አያደርጋቸውም። "
ሌላው የፖለቲካ አቀንቃኝና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አቶ ሚኪኤል አለማየሁ በተለይም በአማራና በትግራይ ሕዝብ መካከል ግንኙነቱን የማጠናከር ስራ መጀመር እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። "ፖለቲከኞቹ ዱላውን ለሕዝቡ ይመልሱለትና ሕዝቡ የሚያደርገውን ያውቃል" በማለትም አክለዋል። 
ሕዝብ በሕዝብ ላይ የጥላቻ መንፈስ ያሳድራል የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለጹት አቶ አዲሱ ጌታነህ ፖለቲከኞች በፈጠሩት ግጭት የተፈጠረውን ቁርሾ ለማሻር ግን ከሐይማኖት አባቶችና የሐገር ሽማግሌዎች ብዙ ይጠበቃል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
"የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኝነቱን ለማጠናከር የሚያስችል ቅርጽ ስለሌለው በአዲስ ቅርጽ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት መጀመር አለበት" በማለት አስተያየታቸውን ያሳረጉት ደግሞ ፕሮፌሰር መድሃኔ አስመላሽ ናቸው።

Illustration Nobelpreis Frieden


ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ነጋሽ መሐመድ

ሽዋዬ ለገሰ