1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

የግብርና ኢንቨስትመንት መድረክ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2016

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ1300 በላይ ባለሀብቶች መሬት የተረከቡ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ሳይገኝ መቆየቱ ተገለጸ። ባለሀብቶች የተሳተፉበት ክልል አቀፍ የግብርና ኢንቨስትመንት መድረክ ትናንት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/4essj
የግብርና ኢንቨስትመንት መድረክ በአሶሳ
የግብርና ኢንቨስትመንት መድረክ በአሶሳምስል Negassa Desalegn/DW

የግብርና ኢንቨስትመንት መድረክ

 

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ1300 በላይ ባለሀብቶች መሬት የተረከቡ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ሳይገኝ መቆየቱ ተገለጸ። ባለሀብቶች የተሳተፉበት ክልል አቀፍ የግብርና ኢንቨስትመንት መድረክ ትናንት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል። የመድረኩ ዓላማ መሬት የወሰዱ ባለሀብቶች ሰላም በሰለፈነባቸው አካባቢዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማነቃቃት እና የፈይናንስ ተቋማት ጋር ለማስተሳሰር መሆኑን የክልሉ የመሬትና ሕብረት ሥራ ማደራጃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ ተናግረዋል። መድረኩ የተዘጋጀው በክልሉ የመሬትና ሕብረት ሥራ ማደራጃ ቢሮ፣ የግብርና ሚኒስተርና ጂ.አይ.ዜድ ኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሆነ ተገልጿል። 

 

በባለሀብቶች የተገኘው ውጤት ዝቅተኛ ነው

በቤኒሻንጉል ጉሙዝክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የኢቨስትመንት ሥራ ለማስጀመር ባለሀብቶችና የፋይናንስ ተቋማትን ያሳተፈ የእንቨስትመንት መድረክ ትናንት በአሶሳ ተጀምሯል። የክልሉ የመሬትና ሕብረት ሥራ ማደራጃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ ለአልሚ ባለሀብቶች እስካሁን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት የተላለፈ መሆኑን በመግለጽ፤  ባደረጉት ማጣሪያ ወደ ሥራ የገቡና ውጤት ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ውስን መሆናቸውን አመልክተዋል።

ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ወደ ሥራ ሳይገቡ መቆየታቸውን የገለጹት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ወረዳዎች ሰላም በመስፈኑ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ልማት ባንክና ግብርና ሚኒስቴር የተሳተፉበት የኢንቨስትመንት ጉባኤ መካሄዱን ጠቁመዋል። በኢቨስትመንት ተሰማርተው መሬት የተላለፈላቸው ባለሀብቶች ወደ ሥራ በመግባት እንዲያለሙና ለውጥ እንዲያመጡ በክልሉ መንግሥት እገዛ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።

አሶሳ ከተማ
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አዳራሽ አሶሳ ከተማ ምስል Negassa Desalegn/DW

በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ውስጥ በግብርና ኢቨስትመንት ዘርፍ የተሳተፉት አቶ ጆቫኒ ሀብቴ ገብርኤል በአካባቢው የነበረው የሰላም እጦት በመቀረፉ ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በካማሺ ዞን ዛይ የተባለ ወረዳ ውስጥ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በእርሻ ኢንስትመንት ተሰማርተው የሚገኙ አቶ ተሾሜ ደሳለኝ በበኩላቸው በ2011 ዓ.ም በአካባቢው የጸጥታ ችግር መከሰቱን ተከትሎ ሥራው ተቋርጦ እንደነበር ገልጸዋል። በወቅቱም የተለያዩ ሥራ መሳሪያዎች እንደወደሙባቸው በመግለጽ ሥራውን ለመጀመር በባንክ በኩል የነበረው ዕዳ እንዲሰረዝላቸውና የወደሙ ማሽነሪዎችም እንዲተኩላቸው ጠይቀዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሁኑ ወቅት ለ1312 ባለሀብቶች በእርሻ ኢንቨስትመንት 523,292 ሄክታር መሬት መተላለፉን የክልሉ የመሬትና ሕብረት ሥራ ማደራጃ ቢሮ መረጃ ያመለክታል። በክልሉ ከእርሻው ዘርፍ በተጨማሪ በማዕድንም እንዲሁ በርካታ ባለሀብቶች መሰማራታቸው ተገልጿል።

ነጋሳ ደሳለኝ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ