1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፌዴራል መንግስት የአማራ ታጣቂዎችን «ከምዕራብ ትግራይ» ለማስወጣት መግባባት ላይ ተደርሷል

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2016

ትግራይ የሚገኙ የጦርነቱ ተፈናቃዮች፥ መንግስት ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው ጥሪ አቀረቡ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በበኩሉ ከጦርነቱ በኋላ በአካባቢዎቹ የተቋቋሙ አስተዳደሮች ባለመፍረሳቸው እና ታጣቂዎች ባለመውጣታቸው ምክንያት ተፈናቃዮች የመመለስ ስራ አስቸጋሪ አድርጎታል ይላል።

https://p.dw.com/p/4eMLs
Getachew Reda
አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትምስል Million Haileselassie/DW

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት በአወዛጊ አካባቢዎች ጉዳይ ላይ ምን አሉ?

በትግራይ የሚገኙ የጦርነቱ ተፈናቃዮች፥ መንግስት ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው ጥሪ አቀረቡ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በበኩሉ ከጦርነቱ በኋላ በአካባቢዎቹ የተቋቋሙ አስተዳደሮች ባለመፍረሳቸው እና ታጣቂዎች ባለመውጣታቸው ምክንያት ተፈናቃዮች የመመለስ ስራ አስቸጋሪ አድርጎታል ይላል። በቅርቡ ከተለያዩ የማሕበረሰብ ተወካዮች በነበራቸው ውይይት የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በምዕራብ ትግራይ፣ ራያ እና ፀለምቲ የተመሰረቱ አስተዳደሮች እንዲፈርሱ እና የአማራ ታጣቂዎች እንዲወጡ መግባባት ተደርሷል ብለዋል።የትግራይና የአማራ ክልሎች ልዩነታቸዉን በዉይይት እንዲፈቱ ነዋሪዎች እየጠየቁ ነው

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት "ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች" ተብለው የሚገለፁት እና ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልል አስተዳደር ስር የነበሩ የምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ ዞን አካባቢዎች ጉዳይ፥ አሁንም አወዛጋቢ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል። ከሰላም ስምምነቱ ዓመት ከመንፈቅ በኃላ ጭምር የጦርነቱ ተፈናቃዮች ያልተመለሱባቸው እነዚህ አካባቢዎች፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በሕገመንግስቱ መሰረት አካባቢዎቹ ወደ አስተዳደሩ እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል። ይህ በአማራ እና ትግራይ ክልል መካከል ውዝግብ የሚነሳበት አጀንዳ፥ በቅርቡ በአፍሪካ ሕብረት አዘጋጅነት ተደርጎ በነበረ የፕሪቶርያው ውል አፈፃፀም ግምገማ ላይም ተነስቶ እንደነበረ፥ የመፍትሔ አቅጣጫ ጭምር እንደተሰጠበት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ በራማ ከተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት አንስተውታል። አቶ ጌታቸው በንግግራቸው በሐይል በተያዙ አካባቢዎች የተመሰረቱ አስተዳደሮች ሊፈርሱ፣ የአማራ ክልል የፀጥታ ሐይሎች ሊወጡ መግባባት መደረሱ አመልክተዋል።የአማራና የትግራይ ክልሎች የወሰን ውዝግብ

በዚህ ረዥም ግዜ የወሰደ የወሰን ይገባኛል ውዝግብ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጦርነቱ ተፈናቃዮች አሁንም በመጠልያዎች የከፋ ኑሮ እንዲገፉ ተገደዋል። ያነጋገርናቸው ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በመቐለ የተለያዩ መጠልያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ አስተዳደር በደረሱት ስምምነት መሰረት ወደቀዬአቸው እንዲመልሷቸው ይጠብቃሉ።

በፌደራል የፀጥታ ሐይሎች እየተጠበቁ ወደቀዬአቸው መመለስ የሚሰጉ ተፈናቃዮች ቢኖሩም፥ ካለንበት ኑሮ አንፃር በሆነ መንገድ ወደቦታችን መመለስ የመጀመርያ ምርጫችን ነው የሚል አስተያየት የሚሰጡም አልጠፉም።

በዚህ የተፈናቃዮች እና የክልሎች ወሰን ጉዳይ ከፌደራል መንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ በቅርቡ ከትግራይ ከተውጣጡ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር በነበራቸው ውይይት ለውዝግቡ ዘላቂ መፍትሔ ህዝበ ውሳኔ መሆኑ መግለፃቸው ይታወሳል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ